1 Samuel 31

የሳኦል መሞት

31፥1-13 ተጓ ምብ – 2ሳሙ 1፥4-12፤ 1ዜና 10፥1-12 1በዚህ ጊዜ ፍልስጥኤማውያን እስራኤልን ወጉ፤ እስራኤላውያን ከፊታቸው ሸሹ፤ ብዙዎቹም በጊልቦዓ ተራራ ላይ ተወግተው ወደቁ። 2ፍልስጥኤማውያን ሳኦልንና ልጆቹን አጥብቀው ተከታተሉ፤ የሳኦልንም ልጆች ዮናታንን፣ አሚናዳብንና ሜልኪሳን ገደሉ። 3ውጊያው በሳኦል ላይ በረታበት፤ ቀስተኞችም ደርሰው እጅግ አቈሰሉት።

4ሳኦልም ጋሻ ጃግሬውን፣ “እነዚህ ያልተገረዙ ሰዎች መጥተው እንዳይወጉኝ፣ እንዳያዋርዱኝ፣ አንተው ሰይፍህን መዘህ ውጋኝ” አለው።

ጋሻ ጃግሬው ግን እጅግ ፈርቶ ስለ ነበር፣ እንቢ አለው። ስለዚህ ሳኦል የራሱን ሰይፍ ወስዶ በላዩ ላይ ወደቀበት።
5ጋሻ ጃግሬውም ሳኦል መሞቱን ባየ ጊዜ፣ እርሱም እንደዚሁ በሰይፉ ላይ ወድቆ አብሮት ሞተ። 6ሳኦልና ሦስቱ ልጆቹ፣ አብረውት የነበሩ ሰዎች ሁሉና ጋሻ ጃግሬው የሞቱት በዚያኑ ቀን ነበር።

7በሸለቆው ማዶና ከዮርዳኖስ ባሻገር ያሉ እስራኤላውያን የእስራኤል ሰራዊት መሸሹን፣ ሳኦልና ልጆቹም መሞታቸውን ባዩ ጊዜ ከተሞቻቸውን ለቀው ሸሹ፤ ፍልስጥኤማውያንም መጥተው ተቀመጡባቸው።

8በማግስቱም ፍልስጥኤማውያን የሞቱትን ሰዎች ለመግፈፍ ሲመጡ፣ ሳኦልና ሦስቱ ልጆቹ በጊልቦዓ ተራራ ላይ ወድቀው አገኟቸው። 9ከዚያም የሳኦልን ራስ ቈርጠው፣ የጦር መሣሪያውንም ገፍፈው፣ የምሥራቹን በየቤተ ጣዖቶቻቸውና በሕዝባቸው መካከል እንዲናገሩ ወደ ፍልስጥኤም ምድር ሁሉ መልክተኞች ላኩ። 10የጦር መሣሪያውን በአስታሮት ቤተ ጣዖት ውስጥ አኖሩት፤ ሬሳውን ደግሞ በቤትሳን ግንብ ላይ አንጠለጠሉት።

11የኢያቢስ ገለዓድ ሰዎች ፍልስጥኤማውያን በሳኦል ላይ ያደረጉትን በሰሙ ጊዜ፣ 12ጀግኖቻቸው ሁሉ በሌሊት ወደ ቤትሳን ሄዱ። የሳኦልንና የልጆቹን ሬሳ ከግንቡ ላይ አውርደው ወደ ኢያቢስ አምጥተው አቃጠሉ። 13ከዚያም ዐጥንቶቻቸውን ወስደው በኢያቢስ ባለው የአጣጥ ዛፍ ሥር ቀበሩ፤ ሰባት ቀንም ጾሙ።

Copyright information for AmhNASV